ድሃው ሰውና የወርቅ ቀለበቱ
በካፒቴን ደጀኔ ዋሻካ የተተረከ
በአንድ ወቅት ከሚሰራው ስራ በሚያገኘው ጥቂት ገንዘብ የሚኖር አንድ ምስኪን ልጅ ነበረ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አንድ ሰው ውሻውን ሲደበድብ አይቶ ልጁ “ለምንድነው የምትደበድበው?” ብሎ ሲጠይቀው ሰውየውም “ሥጋ ሰርቆብን ነው፡፡” አለው፡፡
ልጁም “እባክህ ውሻውን ለእኔ ስጠኝ፡፡” ብሎ ለሰውየው ትንሽ ገንዘብ ሰጥቶት ውሻውን ወደቤቱ ይዞት ሄደ፡፡
በሌላ ቀን ደግሞ አንድ ሰው ድመት ሲገርፍ አይቶ ድመቷን ለምን እንደሚገርፋት ሲጠይቀው ሰውየውም “ጫጩቴን በልታብኝ ነው፡፡” አለው፡፡
ከዚያም ልጁ “እባክህ ድመቷን እኔ ልውሰዳት፡፡” ብሎ ወደቤቱ ይዟት ሄደ፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ደግሞ አንዲት ቆንጆ ሴት ስታለቅስ ያገኛታል፡፡ እርሷም “እባክህ አድነኝ፡፡ ጅብ ሊበላኝ እየተከታተለኝ ነው፡፡” አለችው፡፡ (ሰይጣን በሰው ላይ ሲሰፍር የሚያውቀው ጅብ ሲሆን ሰውየውም የቡዳ ተምሳሌት ስለሆነ ጁቡን ሊጋልበው ይችላል፡፡) ለማንኛውም ልጁ ሴትየዋን አዳናት፡፡ ሆኖም ሴትየዋ በሴት የተመሰለች የሰይጣን ልጅ ነበረች፡፡ ስለዚህ የልጁን ውለታ ለመክፈል በመፈለግ አብሯት ወደቤቷ እንዲሄድ ጠየቀችው፡፡
በመንገዳቸውም ላይ በድንገት ልጁን ወደ ባህር ውስጥ ወርውራው አብረው ወደባህሩ ጥልቅ ወረዱ፡፡
ከባህሩ ሥር አባቷን ሊያገኙት እየሄዱ ልጁን “አባቴ ‘እንደምነህ?’ ሲልህ ‘እግዚአብሔር ይመስገን፤ ደህና ነኝ‘ አትበል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ሥም ስለማይወድ ‘አዎ’ ብቻ ካልከው ትሸለማለህ፡፡” አለችው፡፡
እናም ለአባትየው ሰላምታ ሲሰጠው ልጅቷ እንደመከረችው በማድረግ “አዎ፣ አዎ” ብቻ በማለት ሲመልስ የእግዚአብሔርን ስም ግን አልጠራም ነበር፡፡ ልጅቷም ምስኪኑ ልጅ እንዴት ህይወቷን ከጅቦች እንዳተረፈላት ለአባቷ ነገረችው፡፡ “እባክህ የወርቅ ቀለበት - አጥሊ ስጠው፡፡” ብላ ለመነችው፡፡
ይልጅቷም አባት ለምስኪኑ ልጅ የወርቅ ቀለበቱን ሰጠው፡፡ አጥሊ የአስማት ቀለበት ሲሆን ሲጠየቅ የተፈለገውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንደሚችል ለልጁ ነገረችው፡፡
“ሁልጊዜ ከራስህ እንዳትለየው፡፡” ብላ መከረችው፡፡
እሱም “መልካም እንግዲህ፡፡ አጥሊ፣ አሁን ወደቤቴ ውሰደኝ፡፡” ሲለው ወዲያው ልጁ ወደቤቱ ገባ፡፡
“አጥሊ፣ ምግብ ስጠኝ፡፡” ሲለው የተለያየ ምግብ አቀረበለት፡፡ በእንደዚህ ዓይነት እየኖረ ከእለታት አንድ ቀን ለእናቱ የንጉሱን ልጅ ማግባት እንደሚፈልግ ነገራት፡፡
እናትየውም “ይህንን ማድረግ እንዴት ይቻልሃል?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“ግዴለሽም፣ ታያለሽ!” ሲላት እናትየውም በባህሉ መሰረት ወደ ቤተ መንግስቱ ደጃፍ ሄዳ “ንጉስ ሆይ! እባክዎ ልጅዎን ለልጄ!” እያለች ትጮህ ጀመር፡፡
“ምንድነው የምትይው?”
“ልጄ ሴት ልጅዎን ሊያገባ ይፈልጋልና እባክዎ ልጅዎን ለልጄ ይዳሩለት፡፡” ብላ ተማፀነች፡፡
ንጉሱም “እኔ የምጠይቀውን ነገር ሁሉ ማሟላት ይችላል? ወደ ቤተ መንግስቴም ወርቅ አምጥታችሁ ወደ ልብስነት ልትቀይሩት ትችላላችሁ?” አላት፡፡
እናትየውም ወደ ልጇ ተመልሳ የንጉሱን ትዕዛዝ ነገረችው፡፡ ልጁም “ይህንን ማድረግ እችላለሁ፡፡” ብሎ ቃል ገባ፡፡ ከዚያም የወርቅ ቀለበቱን “አጥሊ ሆይ! እባክህ ለልዕልቷ የወርቅ ልብስ ውሰድላት፡፡” ሲለው አጥሊም የተባለውን አደረገ፡፡
በዚህ ሁኔታ ምስኪኑ ልጅ የንጉሱን ልጅ አግብቶ መኖር ጀመረ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አንድ የኔቢጤ ወደ ምስኪኑ ሰው ቤት መጥቶ ምግብ እንዲሰጡት “ስለ እግዚአብሔር ምግብ ስጡኝ፡፡” እያለ ሲለምን በልእልቲቱ ጣት ላይ የወርቁን ቀለበት አየው፡፡ ባሏ ቀለበቱን ለሚስቱ ሰጥቷት በጥንቃቄ እንድትይዘው ነግሯት ነበር፡፡ ነገር ግን የኔቢጤው ቀለበቱን ከጣቷ ላይ ሰርቆ በመውሰድ ወዲያው “እቤቴ ውሰደኝ፡፡” ብሎ ሲያዘው ቀለበቱም ሰውየውን ወደ ባህሩ ወለል ይዞት ሄዶ እንደገና ደሃ ሆነ፡፡
መጨረሻ
ቢያ ዋሬት ባሄ ኬራች
ለእኔ መልካም እንቅልፍ ለአንተ ቁንጫ!
(ይህ ማለት ቁንጮቹ በሙሉ በእኔ ላይ ሳይሆን በአንተ ላይ ይስፈሩ ማለት ነው፡፡)
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|