ብልሁ አታላይ
በካፒቴን ደጀኔ ዋሻካ የተተረከ
በአንድ ወቅት አንድ ሙርቺን የተባለ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው በጣም ብልህ ስለነበረ ሰዎቹን ሁሉ ያታልል ነበር፡፡ የመንደሩም ሰዎች ምን እንደሚያደርጉት ግራ ገብቷቸው ነበር፡፡
ሁሉንም ያታልል ስለነበረና ሰዎቹም በዚህ በጣም ተሰላችተው ስለነበረ “ከእኛ ርቀህ እንድትኖርና ከዚህ በኋላ እንዳታስችግረን ምንድነው ማድረግ ያለብን? ከአንተ ለመገላገል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡” አሉት፡፡
እርሱም “አንዲት ላም አለችኝና እርሷንም ወስዳችሁ ካረዳችኋት በኋላ ቆዳዋን ስጡኝ፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም ላሟን ካረዷት በኋላ ቆዳዋን ሰጡት፡፡ እርሱም ቆዳዋን ወስዶ ካደረቀው በኋላ ወደሩቅ ሃገር ይዞት ሄዶ ደረቁን ቆዳ በመቀጥቀጥ ብዙ ከብቶችን አስደንብሮ ወደ መንደሩ ብዙ ላሞችና በሬዎች ይዞ ተመለሰ፡፡
የመንደሩም ሰዎች በጣም ተገርመው “እነዚህን ሁሉ ከብቶች ከየት አመጣሃቸው?” ብለው ጠየቁት፡፡
እርሱም “ደረቅ ቆዳ በከብቶች የሚቀይር አንድ ሰው አለ፡፡” አላቸው፡፡
በዚህ ጊዜ ሰዎቹ ከብቶቻቸውን በሙሉ አርደው ቆዳቸውን ሊሸጡ ይዘው ሄዱ፡፡ ሆኖም ቆዳቸውን የሚገዛቸው ሰው ስላላገኙ በጣም ተበሳጭተው “ለምንድነው የዋሸኸን? ከብቶች በቆዳ የሚለውጥ ሰው አለ ብለኸን ነበር፡፡” ሲሉት እርሱም “የነገርኳችሁ ነገር እውነት ነው፡፡ ነገር ግን እናንተ የሄዳችሁት ወደ ተሳሳተ ቦታ ነው፡፡” አላቸው፡፡
ይህንንም ሰው ከመንደሩ ሊያስወግዱት ስላልቻሉ “እንግዲህ አንተን እንዴት አድርገን ነው ከዚህ የምናስወግድህ?” ሲሉት “አንዲት ጎጆ አለችኝ፡፡ እርሷን አቃጥሉና አመዱን ስጡኝ፡፡” አላቸው፡፡ እንደተባሉትም አደረጉ፡፡
እርሱም አመዱን በሶስት ስልቻ ሞልቶ በመሄድ ከአንዲት ጎጆ ዘንድ ሲደርስ አመዱን ከደጃፉ ላይ አስቀምጦ ቡና ሊጠጣ ሄደ፡፡ ቡናውን ከጠጣ በኋላ ጩኸቱን ሲለቀው የመንደሩ ሰዎች ሁሉ ወጥተው “ምን ሆነሃል?” ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም “ሶስት ስልቻ ጤፍበኢትዮጵያ ደጋማ ሥፍራዎች የሚበቅል ሰብል ይዤ መጥቼ ነበር፡፡ ሆኖም ጤፉን በሙሉ ወስደው በአመድ ለወጡብኝ፡፡” ሲላቸው እነርሱም “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ቢሉት “እመኑኝ! ጤፍ ነበር ያመጣሁት፡፡ በምትኩ ግን አመድ አኖሩልኝ፡፡ ይህ የሌቦች አገር መሆን አለበት፡፡” እያለ መጮሁን ቀጠለ፡፡
ሰዎቹም ስማቸው እንዳይጠፋ በመፍራት ሶስት ስልቻ ጤፍ ሰጥተውት ጤፉን ይዞ ወደ መንደሩ ተመለሰ፡፡
የመንደሩም ሰዎች እንደተለመደው “ይህንን እንዴት ልታደርግ ቻልክ?” ብለው ሲጠይቁት እርሱም አመድ በጤፍ የሚቀየርበት “አንድ ቦታ አለ፡፡” አላቸው፡፡
“ይህንን እኛም ማድረግ እንችላለን?”
“አዎ”
እነዚያ ሞኝ ሰዎች አመድ ይዘው ቢሄዱም ጤፍ ሳያገኙ ቀሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ውሸታሙ ሰው “ውሃ ውስጥ ወርውሩኝና ልሙት፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም ሰውየውን ውሃ ውስጥ ቢወረውሩትም ዋኝቶ በመውጣት “አልሞትኩም!” አላቸው፡፡
ወደሚቀጥለው > |
---|