አቡ ናዋስ እና ቃዲው
በዩሱፍ አማን ኡስማን የተተረከ
በሃረር አሚኖች ዘመን ሃረር ውስጥ ይኖር የነበረ አንድ አቡ ናዋስ የተባለ ሰው ነበር፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ይህ ሰው በህልሙ ሚስቱን ሲፈታ ይታየውና ከእንቅልፉ ሲነቃ ባየው ህልም በጣም ይደነግጣል፡፡ ሚስቱንም በጣም ይወዳት ነበርና ስለህልሙ ለእሷ ከመንገር ይልቅ ቃዲውን (የእስልምና ዳኛ) ሊያማክር ሄደ፡፡
እንዲህም ብሎ ነገረው “በህልሜ የምወዳትን ሚስቴን ስፈታት አየሁ፤ በመሃከላችን ምንም ዓይነት ጠብ የለም፡፡ ነገር ግን ሚስቴ ለእኔ ጥሩ እድል ወይም መጥፎ እድል የምታመጣልኝ መሆኗን ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡”
ቃዲው ታዲያ የሰውየው ሚስት በጣም ቆንጆ እንደሆነች ያውቅ ነበርና ለራሱ ሊያደርጋት በመፈለግ “ልጄ ሆይ ያለምከው ህልም በጣም እውነት ነው፡፡ ስለዚህ ካሳ ከፍለሃት ልትፈታት ይገባል፡፡” አለው፡፡
አቡ ናዋስ ግን በቃዲው መልስ ስላላመነበትና ድብቅ ፍላጎት ሊኖረው ይችላል ብሎ ስለጠረጠረው ትቶት ሄደ፡፡ ታዲያ በዚህን ጊዜ ቃዲው አቡ ናዋስን የሚያስወግድበትን መላ በመዘየድ ወደ አሚሩ ዘንድ ሄደ፡፡
ከአሚሩም ጋር ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ለአሚሩ “እዚህ የመጣሁት በህልሜ ያየሁትን መልዕክት ለአንተ ላደርስ ነው፡፡ ስለሞቱት ወላጆችህ ህልም አይቼ ስለጤንነትህና ስለኑሮህ ነገርኳቸው፡፡” አለው፡፡ አሚሩም ስለሞቱት ወላጆቹ በሰማ ጊዜ ደስታና ሃዘን የተቀላቀለበት ስሜት ተሰማው፡፡
ቃዲውም “ከአባትህ የተላከ መልዕክት አለ፡፡ ጋቢ በጣም ታማኝ በሆነ ሰው ላክልኝ ብሎሃል፡፡ ጋቢውንም በአስቸኳይ እፈልገዋለሁ ብሎሃል፡፡” አለው፡፡
አሚሩም ለዚህ አደራ ታማኝ የሚሆን ሰው በአእምሮው ቢያሰላስልም ማንንም ማግኘት አልቻለም፡፡ በዚህን ጊዜ ታዲያ ቃዲው ፈጠን ብሎ “ጌታዬ ሆይ፣ ታማኝና ፈጣን ሰው እኔ አውቃለሁ፡፡ ከአቡ ናዋስ የተሻለ ሰው የለም፡፡ ጋቢውንም ለአባትህ ሊያደርስ የሚችለው ብቸኛ ሰው እሱ ነው፡፡” አለው፡፡
አሚሩም በዚህ ሃሳብ ተስማማ፡፡
ስለዚህ አቡ ናዋስ ተጠርቶ አሚሩ ዘንድ ቀረበ፡፡ የዋሁ አቡ ናዋስ ስለተሸረበበት ሴራ ምንም ሳያውቅ ወደ ቤተመንግስት መጣ፡፡
አሚሩ ዘንድም በቀረበ ጊዜ አሚሩ “አቡ ናዋስ ሆይ፣ በጥንቃቄ አድምጠኝ፡፡ እዚህ ያስመጣሁህ ሟቹ አባቴ ጋቢ በጣም ስለሚያስፈልገው ታማኝ ለሆነ ሰው በአስቸኳይ እንድልክለት መልዕክቱን በቃዲው በኩል ስላስተላለፈልኝ ነው፡፡ ስለዚህ አንተ ብቸኛው ታማኝ ሰው በመሆንህ ለዚህ ስራ ተመርጠሃል፡፡ እናም መቼ መቀበር እንደምትፈልግ ንገረኝና ጋቢውን ላዘጋጅ፡፡” አለው፡፡
አቡ ናዋስም ይህ በቃዲው የተሸረበበት ሴራ መሆኑን ወዲያው ስለተረዳ ከዚህ ሴራ የሚወጣበትን ዘዴ በመፈለግ በእቅዱ ተስማማ፡፡ ሆኖም አሚሩ አንድ ውለታ እንዲውልለት ጠየቀው፡፡
“ከአባቴ መቃብር ጎን መቀበር እፈልጋለሁ፡፡” አለው፡፡ ይህንንም ያደረገው ዘመዶቹንና ጓደኞቹን ለመሰናበት ፈልጎ ነበር፡፡
እናም አሚሩን “ይህንን ካደረክልኝ እኔም ትዕዛዝህን እፈፅማለሁ፡፡” አለው፡፡
አሚሩም በዚህ ተስማማ፡፡
ከዚያ በኋላ አቡ ናዋስ ወደ ተዘጋጀለት ክፍል ሄዶ እቅዱን በተግባር ማዋል ጀመረ፡፡ የራሱንም መቃብር ራሱ ቆፍሮ ምልክት ካደረገበት በኋላ ከተቀበረ በኋላ ሊያመልጥ የሚችልበትን ቦይ ውስጥ ውስጡን መሰርሰር ጀመረ፡፡ ይህንንም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ አጠናቀቀ፡፡
በአራተኛው ሳምንት መጨረሻ የአቡ ናዋስን በቁም መቀበር ለማየት በጉጉት ሲጠባበቅ የነበረው ቃዲ ከቤተ መንግስቱ ከማንም ቀድሞ ደረሰ፡፡
አሚሩም ከአማካሪዎቹና ከአጃቢዎቹ ጋር በመሆን ዙፋኑ ወዳለበት ክፍል ገባ፡፡ ወዲያውኑ አቡ ናዋስ ወደ ክፍሉ ገብቶ ተቀመጠ፡፡
ፀጥታም ሰፈነ፡፡ ቃዲውም በዝምታ ቁጭ ቢልም ሳይታወቅበት አቡ ናዋስ የሚናገረውን ነገር ለመስማት ጓጉቶ ነበር፡፡
ከዚያም አቡ ናዋስ ከመቀመጫው ተነስቶ ለአሚሩ እዚያ የመጣው የአሚሩን ፍላጎት ለማሟላት መሆኑንና ይህንንም ያለምንም ፍራቻ እንደሚፈፅም ነገረው፡፡
ከዚያ አሚሩ ጋቢውን ከሰጠው በኋላ ሊናገር የሚፈልገው ነገር ካለ የመጨረሻ ቃላቱን መናገር እንደሚችል ነገረው፡፡ አቡ ናዋስም የመቃብሩን ቦታ ካመለከተ በኋላ ተመልካቾቹን ተሰናበተ፡፡ ከዚያም ከተከፈነ በኋላ ራሱ በቆፈረው መቃብር ውስጥ እስከነጋቢው ተቀበረ፡፡ ከተቀበረም በኋላ አቡ ናዋስ ውስጥ ለውስጥ በቆፈረው ቦይ አድርጎ በሌላ መንደር በኩል በመውጣት ፊቱን፣ ባህሪውንና ሁለነገሩን ቀይሮ እዚያው መንደር ውስጥ እንደ ሌላ ሰው ሆኖ መኖር ጀመረ፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ አሚሩ ወደሚገኝበት ከተማ ሄደ፡፡ አሚሩ ቤትም እንደደረሰ አሚሩ ሲያየው በመደነቅ ከመቀመጫው ተነስቶ ወደ ውስጥ ገብቶ እንዲቀመጥ ጋበዘው፡፡ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ስለመጣበት ጉዳይ መናገር ጀመረ፡፡
እንዲህም አለው “ሁለቱንም ወላጆችህን አግኝቻቸው ልጃቸው አሚሩ ይህንን ጋቢ እንዳደርስ የላከኝ መሆኔን ነግሬአቸው ጋቢውን ለአባትህ ሰጠሁት፡፡ አባትህ በጣም በመደሰት ምርቃቱን ልኮልሃል፡፡ እናትህ በጣም አርጅታለች፤ አባትህ ግን አሁንም ወጣት ነው የሚመስለው፡፡ ከእነርሱ ጋር ለአንድ ሳምንት ከቆየሁ በኋላ ልሄድ ስነሳ አባትህ ላንተ መልዕክት እንዳደርስ ጠየቀኝ፡፡ መልዕክቱም እናትህ በጣም እያረጀች ስለሆነ ሌላ ሴት ማግባት እፈልጋለሁና ሊያጋባኝ የሚችል ቃዲ በአስቸኳይ ላክልኝ የሚል ነው፡፡” አለው፡፡
አሚሩም በአባቱ ሁኔታ በጣም በመደሰት ቃዲው በአስቸኳይ እንዲመጣ አስጠራው፡፡ ቃዲውም በአሚሩ መፈለጉን ሲሰማ ቶሎ ብሎ ወደ ቤተ መንግስት ሄደ፡፡
አሚሩም “አባቴ እንደገና ለማግባት መፈለጉን በአቡ ናዋስ በኩል መልዕክት ላከብኝ፡፡ ስለዚህ አንተም በአስቸኳይ ወደዚያው ሄደህ ጋብቻውን በሸሪአ ህግ መሠረት እንድትፈፅም፡፡” ብሎ ቃዲውን አዘዘው፡፡
ቃዲው ይህንን በሰማ ጊዜ በጣም ከመደንገጡ የተነሳ በድን ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ ቃዲው ከዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚወጣበት ምንም ዘዴ ስላልነበረው አይኑን እያቁለጨለጨ ግራ በመጋባት የሚናገረው ነገር ጠፋው፡፡
ቃዲውም ከሄደበት ዓለም በመመለስ “ዛሬ ማታ ወደቤት ሄጄ ቤተሰቤን እሰናበትና ነገ በጠዋት እመጣለሁ፡፡” አለው፡፡
ከዚያም በአስቸኳይ ወደ ቤቱ ሄዶ ራሱን ከዚህ ጭንቀት የሚያወጣበት መላ ስላላገኘ ሲቅበጠበጥ አደረ፡፡ በመጨረሻም ተስፋ በመቁረጥ እንዲህ አለ “የአሚሩን ፍላጎት አላሟላም፡፡ በአደባባይ መገደሌ እንደሆን አይቀርልኝም፡፡ ስለዚህ በፈቃደኝነት ሄጄ ራሴን ለአሚሩ ብሰጥ ይሻለኛል፡፡”
እናም ወደ አሚሩ ቤት ሄደ፡፡ እዚያም እንደደረሰ አሚሩን ተስፋ በቆረጠና በጎደጎዱ አይኖቹ እንዲሁም በድን በሆነ ፊቱ እየተመለከተው ትዕዛዙን ለማክበር ዝግጁ መሆኑን ነገረው፡፡ ስለዚህ ልክ አቡ ናዋስ እንዲቀበር በፈለገበት ሁኔታ እሱም ተገንዞ ተቀበረ፡፡
የዚህ ተረት ዋና መልዕክት ለወንድሙ በቆፈረው ጉድጓድ ራሱ ገባበት፡፡ አቡ ናዋስም ከሚስቱ ጋር በደስታ ይኖር ጀመር የሚል ነው፡፡
ወደሚቀጥለው > |
---|