ንጋፕና ንያክዊ
በራምሴ ሽዎል የተተረከ
በአንድ ወቅት በአንዲት መንደር የሚኖር ቤተሰብ ነበር፡፡ ባልና ሚስቱም ሶስት ሴት ልጆች ሲኖራቸው አንደኛዋ የሰው ሥጋ የሚበላ ሰው አግብታ ከእነርሱ በጣም ወደራቀ ሥፍራ ሄደች፡፡
ከዚያች የበኩር ልጃቸው በኋላ ሁለት ንጋፕና ንያክዊ የሚባሉ ሁለት ሴት ልጆችን ወለዱ፡፡ ንጋፕ ምንም አይነት ሥራ በቤት ውስጥ መስራት የማትወድ ነጭናጫ ልጅ ነበረች፡፡ በርግጥ በጣም ቆንጆ ነበረች፡፡ ምንም ነገር መስራት አትወድም ነበር፡፡
ንያክዊ የተባለቸው ታናሽ እህቷ ግን ሁልጊዜ ሁሉንም ሥራ በቤት ውስጥ ትሠራ ነበር፡፡ ሰዎቹ ዓሣ ለማጥመድ ሲሄዱ አብራቸው ሄዳ ዓሣውን በመሰብሰብ፤ በወላጆቿ እገዛ አሳዎቹ እቤት ከመጡም በኋላ ከመጠበሳቸውም በፊት በደረቷ ተኝታ አሳዎቹ በጀርባዋ ላይ እንዲከተፉ የምታደርገው እሷ ነበረች፡፡ እየተገረፈች፣ እየተበደለችና በቤት ውስጥ እየተዋረደች ስትኖር ሌላ ምንም ምርጫ አልነበራትም፡፡
በዚህ ሁኔታ ሲኖሩ አንድ ቀን ንያክዊ ሩቅ አገር ሰው በላውን ሰው አግብታ የምትኖረውን የበኩር ልጃቸው ሄዳ እንድትጎበኝ ታዘዘች፡፡ ጉዞዋንም ጀምራ በመጨረሻ ከእህቷ ቤት ደረሰች፡፡
እዚያም ስትደርስ ለተወሰነ ጊዜ ቆይታ ወደ ቤቷ ግን መመለስ አልፈለገችም ነበር፡፡ በደንብ ተግባባቻቸው፡፡ እህቷ ቤት ምንም ችግር ባይኖርም ወደ ቤተሰቦቿ መመለስ ግን ነበረባት፡፡
ያ ሰው በላ የእህቷ ባል አስማተኛ ቢጤ ነበር፡፡
ንያክዊ ወደቤቷ ለመሄድ ስትነሳ ከፊት ከፊቷ ቀድሟት መሄድ ጀመረ፡፡ ራሱንም ጣፋጭ ፍሬ ወዳለው ዛፍ ቀየረ፡፡
“አንቺ ንያክዊ በይ ነይ፤ አልራበሽም እንዴ? ለምንድነው መጥተሸ ከእነዚህ ፍሬዎች አንዱን የማትቀምሺው?” ይላታል፡፡
ንያክዊ ግን “አይ አሁን እየተመለስኩኝ ያለሁት በጣም ልዩ ከሆነ ቤት ስለሆነ በቂ ምግብ በልቻለሁና ሌላ ነገር መብላት ስለማልፈልግ እነዚህን ፍሬዎች መቅመስ አልችልም፡፡” ብላ መለሰችለት፡፡
ዛፉንም ሳትቀምሰው ቀረች፡፡
ሰው በላው ሰውም ከፊት ፊቷ በመሄድ ኮቡ ወደተባለና ከቅቤና ከደረቅ ዓሣ በደንብ ወደተዘጋጀ ምግብነት ራሱን ቀይሮ ከቆንጆ ማንኪያ ጋር ቀረበ፡፡
ከዚያም ሰውየው “መጥተሸ አትቀምሽም? አልራበሽም?” አላት
ንያክዊ አሁንም “አይ ልቀምስህ አልችልም፤ ልዩ ከሆነ ቤት ነው እየመጣሁ ያለሁትና የምፈልገውን ሁሉ ስለበላሁ ምንም አልፈልግም፡፡ እስካሁንም ስላልራበኝ አልፈልግህም፡፡” አለችው፡፡
እቤትም በደረሰች ጊዜ ለሰዎቹ ስለሁሉም ነገር ነግራቻቸው እዚያው ቆየች፡፡
ከተወሰነ ጊዜም በኋላ በወላጆቿ የምትወደደው ንጋፕ በተራዋ የእህቷን ቤት እንድትጎበኝ ተነገራት፡፡ እሷም ወደዚያው በመሄድ ለብዙ ጊዜ ቆየች፡፡ ያገኘችውን ሁሉ በስስት ትበላም ነበር፡፡ ባለጌም ስለነበረች የእህቶቿንም ልጆች ታጉላላቸው ስለነበረ ሰውየውም ይጠላት ጀመር፡፡
በመጨለሻም ወደ ቤቷ ስትመለስ ሰውየው ልክ ለንያክዊ ያደረገውን ሁሉ አደረገ፡፡ ቀድሞ ከፊት ፊቷ እየሄደም ራሱን ወደ ጣፋጭ ፍሬ ዛፍ በመቀየር “ለምን አትቀምሽኝም?” አላት፡፡
እሷም “አዎ እቀምስሀለሁ ምክንያቱም እየመጣሁ ያለሁት ትልልቅ ቡናማ ጥርሶች ካሉትና ሁልጊዜ ቆሻሻ ነገር ከሚበላ ሰው በላ ሰው ቤት ስለሆነ አንተን መቅመስ አለብኝ፡፡” አለችው፡፡
ፍሬውንም ቀምሳ የተወሰነውን በኪሷ ያዘች፡፡
እንደገናም ይኸው ሰው ከፊት ቀድሟት ራሱን ኮብሌያ ወደሚባል ጥሩ ምግብነት በመቀየር “ለምን አትቀምሽኝም ንጋፕ?” ብሎ ጠየቃት፡፡
“አዎ እቀምስሀለሁ፡፡ በጣም ርቦኛልም፡፡ እየመጣሁ ያለሁት ከደደብ ሰው ቤት ነው፡፡ ሰውየው ሁልጊዜ የሚርበው፣ በጣም ስስታምና ባለጌ ሰው በላ ሰው ነው፡፡ አንተን መብላትማ አለብኝ፡፡” አለች፡፡
ይህንንም ካለች በኋላ ምግቡን በላች፡፡
ከሄደችበት ቦታ ብዙ ስለቆየች ወላጆቿ የተገደለች ወይም ከማይታወቅ ሥፍራ ላይ የሞተች ስለመሰላቸው ትመለሳለች ብለው አልጠበቁም ነበር፡፡
ንያክዊ ታጭታ ስላገባች የሰርጓ ዕለት በአጋጣሚ ንጋፕ በተመለሰችበት ቀን ነበር፡፡
ንጋፕም በሰው በላው ሰው እየተበላች ባለችበት ጊዜ ጭንቅላቷ ተቆርጦ ከሰውነቷ በመለየት ወደ ቤት መጥቶ እንዲህ እያለ ይዘፍን ጀመር፤
“ሴት ልጅ ብሆንና ባልበላ ኖሮ
ከብዙ ላሞች ጋር እዳር ነበር
ብዙ የሚያማምሩ ላሞች
በቤተሰቤም ሃብታም እሆን ነበር
ታዲያ እድሌ ከፍቶ አንቺው የኔው እህት ሆንሽ
ልቀልድብሽ አልፈልግም
እባክሽ ያዢኝና
ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልሙት፡፡”
በዚህ ሁኔታ ንጋፕና ንያክዊ መጨረሻቸው እንዲህ ሆነ፡፡ ልጆች መታየት አለባቸው፡፡ ሁሉም ልጆች በቤት ውስጥ ከወላጆቻቸው ጋር የመኖር መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን በታሪኩ ውስጥ ያሉት ወላጆች አንደኛዋን ወደው ሌላኛዋን አግልለዋታል፡፡ ታዲያ እንደ ዕድል ሆኖ በጣም የሚወዷት ልጃቸው አስቸጋሪ በመሆኗና በሥርአት ባለማደጓ ምክንያት በደደብነቷና በመጥፎ ባህሪዋ ምክንያት በድንገት ሞተች፡፡ ስለዚህ ህፃናት በወላጆቻቸው እኩል መታየት አለባቸው፡፡
< ወደኋላ |
---|