አስማተኛዋ ላም
በአጁሎ አኮኝ የተተረከ
በአንድ ወቅት ሁለት ልጆች ያሏት ሴት ነበረች፡፡ ይህችም ሴት ስትሞት ልጆቹ ከባሏ ጋር ቢቀሩም ባሏ ግን ሁለተኛ ሚስት ነበረችው፡፡ ሁለተኛዋም ሚስት በመጀመሪዋ ሚስት ልጆች ደስተኛ ስላልነበረች የአባትየው ህይወት አስቸጋሪ ሆነ፡፡ ሁለተኛዋ ሚስት ልጆቹን ከራሷ ልጆች ጋር ልትመግባቸው አትፈልግም ነበር፡፡
እናታቸው ከመሞቷ በፊት እሷ ስትሞት ምን እንደሚከሰት ስላወቀች ልጆቿን “ጫካ ሂዱና አንድ ምግብ የሚሰጣችሁ ሰው ታገኛላችሁ፡፡” ብላቸው ነበር፡፡
እንደተባሉትም ልጆቹ በድብቅ ወደጫካው በየቀኑ እየሄዱ ምግብ የምትሰጣቸው ላም አገኙ፡፡ በየቀኑም ወደቤት ጠግበው ይመለሱ ነበር፡፡ አባታቸው ግን ስለሚስጥራቸው ያውቅ ነበር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን የሁለተኛዋ ሚስት ልጅ “ዛሬ አብሬያችሁ ወደ ጫካው ሄጄ ምግባችሁን ከየት እንደምታገኙ ማወቅ እፈልጋለሁ::” አላቸው፡፡
እነርሱም “እባክህ ከእኛ ጋር ስትመጣ ትራባለህ እኛ እናት ስለሌለን ሙሉ ቀን ስንዞር ነው የምንውለው፡፡ አንተ ግን ትቸገራለህ::” አሉት፡፡
ሆኖም ልጁ ሃሳቡን ስላልቀየረ አብረው ይዘውት ሄዱ፡፡ ላሚቷ ያለችበት ሥፍራ ከቤታቸው በጣም ሩቅ ቦታ እንደደረሱም ታላቅየው ልጅ ላሟ ያለችበትን ላለማሳየት ዙሪያውን ቢያዞራቸውም ታናሽየው ስለራበው ታላቁ “እሺ በቃ ላሟን እንጥራት” ብሎ ላሟን ጠርተው ላሟ የሰጠቻቸውን ምግብ በሙሉ ሶስቱም አብረው በሉ፡፡
ወደቤታቸውም ሲመለሱም የሁለተኛዋ ሚስት ልጅ ለእናቱ “እማዬ ሚስጥራቸውን ደርሼበታለሁ፡፡ ምግባቸውን የሚያገኙት ጫካ ውስጥ በድብቅ ከምትኖር አንዲት ላም ነው፡፡” ብሎ ነገራት፡፡
ሴትየዋም ስለሁኔታው ባሏን ጠየቀችው፡፡ በመቀጠልም “እኔ አሁን ነፍሰ ጡር ነኝ፡፡ እናም የልጆችህ ላም እዚህ እንድትመጣልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ላሚቷ እዚህ ካልመጣች ልጃችን አያድግም፡፡” አለችው፡፡
ባልየውም “እኔ ላም የለኝም::” አላት፡፡
“እሷም ሚስጥራችሁን ስለደረስኩበት ላሚቷን እዚህ አምጣት፡፡” አለችው፡፡
ላሚቷ እንድትመጣ በጣም አጥብቃ ስለጎተጎተችው በመጨረሻ እሱም ተረትቶ ላሚቷ እንድትመጣ ተደረገ፡፡
ላሚቷ ቤት እንደደረሰችም ሴትየዋ “ላሚቷን እረዱልኝ ምክንያቱም ነፍሰ ጡር ስለሆንኩ ሥጋ ያስፈልገኛል፡፡” አለች፡፡ ሆኖም ላሚቷን ሊያርዷት ቢሞክሩም አልቻሉም፡፡
ሴትየዋም “ይህች ላም ካልታረደች እነዚህን ሁለት ልጆች እገድላለሁ፡፡” አለች፡፡
በመጨረሻም ቃል ገብተው ላሚቷ ታረደች፡፡ ሆኖም ቆዳዋን ሊገፏት ሲሞክሩ አልገፈፍ አላቸው፡፡
አሁንም ሴትየዋ “ቆዳዋ ካልተገፈፈ እነዚህን ሁለት ልጆች እገድላለሁ፡፡” ብላ በማስፈራራቱ ቀጠለችበት፡፡
እንደገና ሲሞክሩ በዚህን ጊዜ ቆዳው ተገፈፈላቸው፡፡ ሆኖም ሥጋውን ሊቀቅሉ ቢሞክሩም አልበስል አላቸው፡፡
“ሥጋው ካልተቀቀለ ልጆቹን እገድላቸዋለሁ፡፡”
ከዚያም ሥጋውን ማብሰል ቻሉ፡፡ ነገር ግን ሥጋውን ለማብረድ ድስቶቹን ከእሳቱ ላይ ለማውረድ ሲሞክሩ ማንሳት አቃታቸው፡፡
“ድስቶቹን ከእሳቱ ላይ ካላወረዳችሁ ልጆቹን እገድላቸዋለሁ፡፡” አለች፡፡
በጣም ፈርተው ስለነበረ ድስቶቹን እንደምንም ብለው አወረዷቸው፡፡ ከዚያም ስጋው ተበላ፡፡ ሆኖም ሁለቱ ልጆች ምግብ የሚሰጣቸው ስላልነበረ ችግር ላይ ወደቁ፡፡ የእንጀራ እናታቸውም ልትገድላቸው ትፈልጋለች፡፡ ላማቸውም ተቀቅላ ተበልታለች፡፡ ስለዚህ ከቤት ጠፍተው ጫካ ገቡ፡፡
ሁለቱ ልጆችም በድንገት ተለያይተው ለየብቻ አደጉ፡፡ ትልቁ ልጅ አንድ መንደር አግኝቶ እዚያው ሲኖር ጫካ ውስጥ የሚገኝ የአንድ መንደር አለቃ ከሆነች ልጅ ጋር የድብቅ ፍቅር ያዘው፡፡ ልጅቷም አንድ መኪና ሰጥታው ከሚኖርበት መንደር እርሷ ወደምትኖርበት መንደር እየተመላለሰ ይጎበኛት ጀመር፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን እርሱ በሚኖርበትና ፍቅረኛው በምትኖርበት መንደሮች መሃከል ጦርነት ተነስቶ ጠላቶች የመንደሩ አለቃ የሆነውን የልጅቷን አባት ሊገድሉት ተነሱ፡፡
ልጁም በድብቅ ማታ ማታ የልጅቷን መንደር ሰዎች ይረዳቸው ነበር፡፡
የመንደሩም አለቃ ተገርሞ “ይህ ማታ ማታ የሚረዳኝ ሰው ለመሆኑ ማነው?” ብሎ ጠየቀ፡፡ ምክንያቱም አንድ እንግዳ ሰው ከእርሱ ወገን በመሆን በጥንካሬ ሲዋጋ አይቶት ነበር፡፡
ለተከታዮቹም “ጦርነቱ ማታ ማታ ሲጀመር ሁልጊዜ ከእኛ ወገን ሆኖ የሚረዳን አንድ ሰው አለ፡፡” ብሎ ነገራቸው፡፡
እነርሱም “እስኪ ስብሰባ ጠርተን ሁሉም ሴት ልጆችህን እንዲገኙ እናድርግ፡፡” አሉት፡፡
እርሱም ይህንን አደረገ፡፡
ሴት ልጆቹንም “እያንዳንዳችሁ ሄዳችሁ ባሎቻችሁን ወይም ፍቅረኞቻችሁን ይዛችሁ መጥታችሁ በህዝብ ፊት አሳዩኝ፡፡” አላቸው፡፡
እነርሱም እንደተባሉት አደረጉ፡፡ አንደኛዋ ግን ወደ እንግዳው ሰው በሄደች ጊዜ ሰውየው ፈንጣጣ ይዞት ዝንቦች ወረውትና ከሰዎች ተገልሎ ብቻውን ቁጭ ብሎ አየች፡፡
የአለቃው ልጅ ፍቅረኛዋን እጁን ልትይዘው ቀረብ አለች፡፡ አለቃው ይህንን ባየ ጊዜ “አንቺ መጥፎ ልጅ ነሽ፡፡ እንዴት ፈንጣጣ የያዘው ሰው ትመርጫለሽ? እሱ ባልሽ ሊሆን አይችልም፡፡” ብሎ ጮኸባት፡፡
እሷም “እሱ ፍቅረኛዬ ነው፡፡ አፈቅረዋለሁ፤ ላገባውም እፈልጋለሁ::” አለች፡፡ በዚያች ቅፅበት የአለቃው ጭንቅላት አበጠ፡፡ ሰዎቹም ፍላጎቷን ተቀበሏት፡፡ ስለምትወደውም ታግባው አሉት፡፡
ልጅቷም “እሱን ካለተቀበልከው ጭንቅላትህ እንደገና ወደነበረበት አይመለስም፡፡” አለችው፡፡
በመጨረሻም አለቃው የህዝቡን ምክርና የልጁን ቃላት ተቀብሎ ጭንቅላቱ ወደነበረበት ሲመለስ እንግዳው ሰውም የልጅቷ ባል ሆነ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|