ዓሣን በረጅምና ቀጭን ጦር ማጥመድ
በአክዋይ ጎራ የተተረከ
ሴቶች ዓሣዎችን በጦር ሲያድኑ ያየ አንድ ሰው ከዛፍ ላይ ተደብቆ ይመለከት ነበር፡፡ የያዙትን አንድ ዓሣ አንደኛዋ ጭንቅላቱን ሁለተኛዋ ደግሞ ጭራውን ይዘው መጓተት ጀመሩ፡፡ ዓሣውን ግን በጦር የወጋችው ሁለተኛዋ ሴት ነበረች፡፡ በዚህን ጊዜ ሰውየው ከዛፍ ላይ ተጣርቶ “አትጣሉ አዳምጡኝ::” አላቸው፡፡
በዚህን ጊዜ ዝም ብለው ያዳምጡት ጀመር፡፡
ከዚያም “ማነው የወጋው?” ሲላቸው የዓሣውን ጭራ የያዘችው ሴት “እኔ ነኝ ቀድሜ የወጋሁት፡፡” አለች፡፡
ሰውየውም “አንቺ ጭንቅላቱን የያዝሽው ሴት ዓሣውን ልቀቂው::” አላት፡፡ ሆኖም ዓሣውን ስለፈለገችው ለመተው ፈቃደኛ አልሆነችም፡፡
ሰውየውም “እባክሽ ስለእኔ ብለሽ ዓሣውን ልቀቂው::” አላት፡፡ ከዚያም ልመናውን ሰምታ ስትለቀው ከሌላኛዋ ሴት እጅ አሟልጮ ወደ ወንዙ ውስጥ ስለገባ ሁለቱም ሳያገኙት ቀሩ፡፡
ሰውየውም “ዓሣው የታለ?” ሲላቸው እነርሱም “አመለጠ” አሉት፡፡
ከዚያም “አደናችሁን ቀጥሉ::” አላቸው፡፡ (ይህም ማለቱ ምግባቸውን ለማግኘት መሥራት እንዳለባቸው ሊነግራቸው ነው፡፡)
ሴቶቹ ወደቤት ሲመለሱ “አንድ የማይታይ ሰው ነው ፍርዱን የሰጠን::” ብለው ለሌሎች ሁሉ ተናገሩ፡፡
አሁንም ደግመው ዓሣ ለማጥመድ ሲሄዱ ተመሣሣይ ነገር ተደገመ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ጭንቅላቱን የያዘችው ሴት ነበረች ትክክለኛዋ የዓሣው ባለቤት፡፡ ስለዚህ ሰውየው ጭራውን የያዘችውን ሴት እንድትለቀው ነገራት፡፡ እሷም ስትለቀው ጭንቅላቱን የያዘችው ሴት ዓሣው ሳያመልጣት በቀላሉ ስንጥቡን ይዛ አስቀረችው፡፡
ሰውየውም “ዓሣው አመለጠ?” ብሎ ጠየቀ፡፡
እሷም “አላመለጠም፡፡” ብላ መለሰች፡፡
“እንግዲያው አደናችሁን ቀጥሉ::” አላቸው፡፡
እነርሱም እንደተባሉት አደረጉ፡፡ ከዚያም ወደ መንደራቸው ተመልሰው የሆነውን ለሰው ሁሉ ነገሩ፡፡
ስለዚህ የመንደሩ ሰው በሙሉ የዚህን ድብቅ ድምፅ ባለቤት ሊፈልግ መጣ፡፡
እንደደረሱም ግማሾቹ ዓሣ ሲያጠምዱ ግማሾቹ ደግሞ ተደብቀው የድምፁን አቅጣጫ ሲጠባበቁ ከዛፉ ላይ እንደሚመጣ ስላዩ ሰው መሆኑን አውቀው ሰውየውን ከዛፉ ላይ እንዲወርድ ነገሩት፡፡ ይዘውትም ወደ መንደሩ እየወሰዱት ሣለ በምትሃት ራሱን ቀይሮ እንስሳ በመሆን አንዴ ጥቁር፣አንዴ ነጭ፣ አንዴ እፅዋት፣ አንዴ ደግሞ ሴት፣ እየሆነ ቢቀያየርባቸውም ሳይለቁ ይዘውት ወደ መንደሩ አመጡት፡፡ ከዚያም ለብቻው አንድ ጎጆ ሰጥተውት ምግብ ግን በመከልከል አስማተኛ ሰው መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ወሰኑ፡፡ እሳት ውስጥ እንዳይወድቅ አንዲት ጠባቂ ልጃገረድ አኖሩለት፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን ምግብ ይሰጡት ጀመር፡፡
ልጅቷም ለብዙ ቀናት አብራው እየተኛች ቆይታ ድንገት ጠፍቶ ወደ ወንዙ ዳርቻ ተመልሶ ሄደ፡፡ በዚህ ጊዜ ልጅቷ አርግዛ ነበር፡፡
ወንድ ልጅም ተወለደ፡፡ ነገር ግን ህጻኑ ቢበላ የማይጠግብና በጣም ወፍራም ትልቅና ጠንካራ ሆኖ አደገ፡፡ ነገር ግን አባቱ የማይታወቅና ስም የሌለው በመሆኑ ልጁ ኦንጌ የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡ ይህም ማለት የእንግዳው ሰው ልጅ ማለት ነው፡፡ ልጁም ሲያድግ ጠንካራ በመሆን የአኙዋክ ህዝብ ንጉስ ሆነ፡፡
ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ንጉሱ ኦንጌ እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡
እስካሁንም ድረስ የአኙዋክ ነገስታት አብዛኛውን ጊዜ በእናታቸው ሥም የሚጠሩ ሲሆን ለምሳሌ የኦባንግ ልጅ ተብሎ ይጠራል፡፡ (ኦባንግ የእናቱ ሥም ነው)፡፡ በተጨማሪም አጎቶች የእህቶቻቸውን ልጆች በጣም ሲወዷቸው የአባትየው ስም ሳይሆን የእናታቸው ስም ነው የሚጠራው፡፡
ሌላው የነገስታት ስም ከወንዙ የመጣ የሚል ነው፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|