የተራበው እባብ
በኦፒው አምዎንግ የተተረከ
በአንድ ወቅት ለብዙ ቀናት ምግብ ያልበላ እባብ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ከስቶ ነበር፡፡ ምግብ ለመፈለግም ከጫካው ወጥቶ ዞር ዞር ሲል ከአንድ ገበሬ ቤት ደረሰ፡፡ ከጠርሙስ ውስጥም ወተት ስለተመለከተና በጣምም ከስቶ ስለነበር ጠርሙሱ ውስጥ ተስቦ በመግባት ወተቱን በሙሉ ጠጣው፡፡ በዚህን ገዜ በጣም ስለወፈረ ተመልሶ መውጣት አቃተው፡፡
ገበሬውም ወደ ቤት ተመልሶ ሲመጣ እባቡን ጠርሙስ ውስጥ አይቶት እንዲህ አለው “ጠርሙስ ውስጥ የነበረው ወተት የት ሄደ? የጠጣኸውን ሁሉ ተፍተህ ከጠርሙስ ውስጥ አትወጣም?”
እባቡም “እድሜዬን ሁሉ ሰዎችን ስነድፍ ቆይቻለሁ፤ አሁን ግን ምን ማድረግ እችላለሁ?” ብሎ መለሰ፡፡
በመቀጠልም እባቡ እንዲህ ብሎ አሰበ “ወተቱን ሁሉ ተፍቼ ከጠርሙሱ ብወጣ፣ ገበሬው ይገድለኛል፤ እንደተራብኩም እቆያለሁ፤ ስለዚህ እዚሁ ሆኜ ብሞት ይሻለኛል፡፡” ብሎ እዚያው ጠርሙስ ውስጥ ሞተ፡፡
ሁለት መጥፎ ምርጫዎች ቢገጥሙህ ከሁለቱ የተሻለውን ክፉ ነገር ምረጥ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|