አለቃ ገብረሃና እና ብልኋ ሴት
በወርቁ አለሙ የተተረከ
በአገራችን አንድ ብልህና ታዋቂ የነበሩ አለቃ ገብረሃና የተባሉ ሰው ነበሩ፡፡ እኝህ ሰው ታዲያ ከእርሣቸው የተሻለ ብልህ ሰው ሁልጊዜ ይፈልጉ ነበር፡፡
ሆኖም ብዙ ጊዜ አይሳካላቸውም ነበርና ከእርሳቸው የተሻለ ብልህ ያለ አይመስላቸውም ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ከእርሳቸው የተሻለች ብልህና አዋቂ ሴት አለች መባሉን ሰምተው ወደሷ መንደር በመሄድ ቤቷን አፈላልገው አግኝተውት በእንግድነት ተስተናገዱ፡፡
ቤቱም የሴትየዋ ወላጆች ቤት ነበርና በባህሉም መሠረት አንድ እንግዳ ሲመጣ እግሩን ማጠብ፣ ምግብ ማቅረብ፣ አልጋ ማንጠፍና የመሣሠሉትን በማድረግ እንግዳውን መቀበል ልማድ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በብልኋና በአዋቂዋ ሴት እንዲሁም በወላጆቿ አለቃ ገብረሃና አስፈላጊው መስተንግዶ ሁሉ ተደረገላቸው፡፡
በመጨረሻ ሴትየዋ አለቃን ለሰገራ ይዛቸው እንድትወጣ ተነሯት ፊት ፊት እየመራቻቸው ቤቱን ብዙ ጊዜ አዞረቻቸው፡፡ በመጨረሻም አለቃ ስለደከማቸው ወደ ደጃፉ ሄዱ፡፡ የልጅቷም ቤተሰቦች “ምን ሆኑ? ለምንድነው ወደ ሜዳው ያልወረዱት?” ብለው ቢጠይቁ ብልኋም ሴት “እምቢ ብለው እዚህ አደረጉት፡፡” ብላ መለሰች፡፡
ሁሉም ሰው ስቆባቸው አለቃ ገብረሃና ስለተናደዱ ወደ መኝታቸው ይሄዳሉ፡፡ ብልኋም ሴት አልጋቸውን እንድታነጥፍላቸው ሲነግሯት መደባቸው ላይ ትንሽ ድብዳብ ጣል አድርጋ ልትወጣ ስትል አለቃ “አልጋዬን ለምን በደንብ አታዘጋጅልኝም? ይህ ለአንድ ሰው ይበቃል እንዴ?” ብለው ቢጠይቋት እሷም “እንግዲያው ይህንን ሲጨርሱ ሌላ እጨምርልዎታለሁ፡፡” አለቻቸው፡፡
እሳቸውም ምንም ምርጫ ስላልነበራቸው እዚያችው ድብዳብ ላይ ተኝተው አደሩ፡፡
በማግስቱም ጠዋት ቂም ይዘው ወደቤታቸው ተመለሱ፡፡ ከዚያም ሁለት ቁምጣ ጤፍ በሁለት አህዮች ጭነው ይልኩላትና የጤፉን ብዛት እንድትነግራቸው ይጠይቋታል፡፡ እሷም ለመቁጠር ብትሞክር እርሳቸው ስለሚያሸንፏት ሞኝ ልትባል ሆነ፡፡
ስለዚህ እንዲህ ብላ መለሰች “ጤፉን ቆጥሬ የአህዮቹን ፀጉር ብዛት ያክል ሆኗል፡፡ ስለዚህ የአህዮቹን ፀጉር ቆጥረው ብዛቱን ይድረሱበት፡፡”
በዚህም ጊዜ እሷ በጣም ብልህ ሴት እንደሆነች ተገነዘቡ ይባላል፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|