ሶስቱ
በመሃመድ አሊ አኪቶይ የተተረከ
አንበሣ፣ጅብና ቀበሮ ያአዳኝ ቡድን መስርተው ሁልግዜ አብረው ያድኑ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን እያደኑ ሳለ አንበሳው ግመል ሲይዝ፣ ጅቡ ላም እንዲሁም ቀበሮ ፍየል ያዙ፡፡
ወደቤታቸው በመመለስ ላይ እንዳሉ እረፍት ሊወስዱ ፈልገው ጅቡ መተኛች ሲፈልግ ቀበሮ እንዲህ አለው፡፡ “እንደምታውቀው አንበሳው ሁልግዜም ለራሱ ያደላል፤ በጣም ጠንካራ ስለሆነ ብቻ እሱ ግመሉን ይበላል፣ አንተ ላሟን ትበላለህ፣ እኔ ደግሞ አንዲት ትንሽ ፍየል ብቻ ትደርሰኛለች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም አደን ልሂድና ከቀናኝ እኔና አንተ እንካፈላለን፡፡”
ይህንን ካለ በኋላ ቀበሮ ሁሉንም ነገር ለጅቡ ትቶ ሄደ፡፡ አንበሳውም ከእንቅልፉ ሲነቃ እንዲህ አለ፡፡ “እኔ ርቦኛል፤ ምግቡን እንዴት ብንከፋፈል ትፈልጋለህ?”
ጅቡም “እንግዲህ አንተ ግመል ስለያዝክ ግመሉን ብላ፤ እኔ ላም ስለያዝኩ ላሚቷን እበላለሁ፤ ቀበሮውም ፍየሏን መብላት ይችላል፡፡” አለው፡፡ አንበሳውም እንዲህ አለ፡፡ “አንተ ቀልደኛ ፍጥረት፤ ማደንና መያዝ የቻልከው እኔ በአካባቢው ስላለው እኮ ነው፡፡ እንዴት ምግቡን ለሶስት እንከፋፈለው ብለህ በድፍረት ትናገራለህ?” ብሎ ጅቡን ጭንቅላቱ ላይ ሲመታው አናቱ ከላዩ ላይ ተነቅሎ ዛፍ ላይ ተንጠለጠለ፡፡ ከዚያም ቀበሮው እንዳያይ አንበሳው የሞተውን ጅብ ቀበረው፡፡ ቀበሮውም ከአደኑ ሲመለስ የጅቡን ጭንቅላት ከሩቅ ሆኖ ዛፉ ላይ ያየዋል፤ ሆኖም አንበሳው “እንግዲህ አቶ ቀበሮ ምግቡን እንዴት እንካፈል ትላለህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡
ቀበሮውም እንዲህ አለ፡፡ “በቅድሚያ የእኔን ምክር በመጠየቅህ ኩራት ይሰማኛል፡፡ አንተ ደግሞ የጫካው ንጉስ ነህ፡፡ የፈለከውን ልትወስድ ትችላለህ፡፡ የእኔን ምክር ከፈለግክ ግን ልሰጥህ እችላለው፡፡”
አንበሳውም “አዎ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ንገረኝ” አለው፡፡
ቀበሮውም “እንግዲያው ግመሉን ለቁርስ፣ ላሟን ለምሳ እንዲሁም ፍየሏን ለእራት ብትመገብ ጥሩ ይመስለኛል፡፡” አለው፡፡
አንበሳውም አንተስ ምን ትበላለህ?” ብሎ ጠየቀው::
ቀበሮውም እንዲህ አለ “አይ ምንም ችግር የለም፡፡ እኔ ካንተ የተራረፈውን እበላለሁ፡፡”
አንበሳውም “ድሮ ደደብ ነበርክ፡፡ እንዴት ነው ብልህ ሆነህ እንደዚህ ያለ ብልህ መልስ ልትሰጠኝ የቻልከው?” ብሎ ጠየቀው፡፡ ቀበሮውም “እንደዚህ ብልህ የሆንኩት የራሴንም ጭንቅላት ብቻ ሳይሆን የጅቡንም ጭንቅላት ተጠቅሜ ነው፡፡” ብሎት እየሮጠ ሄደ፡፡
< ወደኋላ | ወደሚቀጥለው > |
---|