አይን አፋር አትሁን
በሁኩን ሁሴን ፉራ የተተረከ
በአንድ ወቅት መሃመድ ሃሰን የተባለ አንድ ልጅ ነበር፡፡ እናትና አባቱም በህፃንነቱ ሞተውበት ነበር፡፡ እነርሱም አንድ መቶ ግመሎች፣ አንድ መቶ ሃያ ፍየሎችና፣ ሰማንያ ላሞች ስለነበራቸው ይህ ሁሉ ሃብት እናትና አባት የሌለው የመሃመድ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ ስመ ሞክሼው የአባቱ ወንድም አጎቱ መሃመድ የልጁ ሞግዚት በመሆን ንብረቱን ሁሉ የራሱ አደረገ፡፡ አጎቱ ድሃና ሁለት ላሞች ብቻ የነበሩት ሲሆን አምባሮ ከምትባለው ሚስቱ ጋር አራት ሴት ልጆች ነበራቸው፡፡ መሃመድ ታዲያ ከአጎቱ ሚስት ከአምባሮ ጋር አይስማማም ነበር፡፡ሁልጊዜ ስትጮህበትና ስትበሳጭበት ግራ ቢጋባም ስለዚህ ጉዳይ ለአጎቱ ትንፍሽ ብሎ አያውቅም ነበር፡፡
መሃመድ የአጎቱን ልጆች ከብቶቹን፣ፍየሎቹንና ግመሎቹን በመጠበቅ ያግዛቸው ነበር፡፡ በተለይም ዴካ የምትባለውን የአጎቱን የበኩር ልጅ ስትወድቅ እያነሳት፣ ስትጎዳ እያፅናናትና ቁስሏ ላይ ቅጠል እያደረገላት አለበለዚያም ምርኩዝ እየቆረጠላት ይንከባከባት ነበር፡፡ ሌሎቹ ልጆች ሁለቱንም ባይወዷቸውም እነዚህ ሁለቱ ግን ጓደኞች ነበሩ፡፡ ዴካ አድጋ የቤቱን ስራ መስራት በጀመረችበት ጊዜ መሃመድ በአጎቱ ሚስት ይራብ ስለነበረ ዴካ ለእርሱ ለየት ያለ ምግብ አዘጋጅታ በመደበቅ ማታ ማታ ሹልክ ብላ እየወጣች ትሰጠው ጀመር፡፡ በኋላም ስላፈቀረችው በጣም ደስተኛ ሲሆን ምንም እንኳን የአጎቱ ሚስት አሁንም ብትጠላውና እንዲሄድ ብትፈልግም እርሱ ግን በእርሷ መበሳጨቱን አቆመ፡፡
እድሜውም በደረሰ ጊዜ ማግባት እንደሚፈልግ ለአጎቱ ነገረው፡፡ አዛውንቶቹም በተሰበሰቡበት አጎቱ “መሃመድ ብዙ ሃብት ወርሶ የነበረ ሲሆን በየጊዜውም ሃብቱ እየጨመረ ሄዷል፡፡ አሁን ደግሞ ሚስት ማግባት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ አንዲት ልጃገረድ ከመንደሩ መምረጥ ስለሚፈልግ የምትሆነውን ሚስት ፈልጌ ላጋባው ዝግጁ ነኝ፡፡” አላቸው፡፡
እናም ሚስት ሊፈልጉለት ተስማሙ፡፡ ሆኖም አምባሮ “አይሆንም! አይሆንም!” ብላ በመጮህ ከባሏ ጋር ተጣላች፡፡ እንዲህም አለች “የወረሳቸው እንስሳት ሁሉ የእርሱ አይደሉም፡፡ ተንከባክበህ ስላሳደከው በቁጥር የጨመሩት ከብቶች ሁሉ ያንተ ናቸው፡፡ እርሱ ልጅ ስለሆነ እንዴት ሁሉንም ይወስዳል?”
አዛውንቶቹም ሁሉ መሃመድ ልጃቸውን እንዲያገባ ፈለጉ፡፡ “ይህ ሁሉ ንብረት ያለው ልጅ! እናትና አባት የሌለው ልጅ!” እያሉ በሃብቱ ስለጎመዡ ሁሉም ሊወስዱት ፈለጉ፡፡
አጎቱም ሚስቱን በቁጣ ተቃውሞ “ንብረቱ በሙሉ የእርሱ ነውና ከፈለገ ሊወስደው ይችላል፡፡” አላት፡፡ በመጨረሻም ግማሹ ንብረት የልጁ እንዲሆን ወስነው በንብረቱ እንዲያገባ ተስማሙ፡፡ በጭቅጭቁም ምክንያት ልጁ ግማሽ ከብቶቹን ወስዶ የእናቱ ዘመዶች ወዳሉበት መንደር ለመሄድ ወሰነ፡፡
“ሚስት እዚያ ማግባት እችላለሁ፡፡ ንብረቴን እዚያ ወስጄ እራሴ እየተቆጣጠርኩ ለማግባት ዝግጁ ስሆን አገባለሁ፡፡” አለ፡፡
ይህንንም ብሎ ሲሄድ ገና መንደሩን ለቆ እንደወጣ ዴካ በጠና ታመመች፡፡ ለሶስት ዓመታት በጠና ታማ ለመሞት ተቃረበች፡፡ ታዲያ አንድ ቀን መሃመድ ከአጎቱ መንደር የመጣ ሰው አግኝቶ ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ “መንደሩ እንዴት ነው? አጎቴና ቤተሰቡስ?” ብሎ ጠየቀ፡፡
ሰውየውም “እነርሱ ደህና ናቸው፡፡ ዴካ ግን አንተ መንደሩን ለቀህ ከሄድክ ቀን ጀምሮ በጣም፣ በጣም ታማለች፡፡” አለው፡፡
እርሱም “አይይ! ያቺ ሴት ለኔ በጣም ደግ ነበረች፡፡ ሁለት በጎች ሸጬ ልጠይቃት ይገባል፡፡” ብሎ ሁለቱን በጎች ወስዶ ከሸጠ በኋላ ገንዘቡን ይዞ ሊጠይቃት ወደ መንደሩ ሄደ፡፡ ልብሶችም ገዛላት፡፡ ወደ መንደሩም ሲቃረብ (እርሷ ከመንደሩ አቅራቢያ ካለ ዛፍ ስር ተኝታ ስለነበረ) በመንገዱ ሲመጣ አየችው፡፡ አጠገቧም ሲደርስ በጣም ደስ ስላላት ከተኛችበት ተነስታ ቁጭ በማለት ሰላምታ ሰጠችው፡፡ እርሱም በጣም መክሳቷንና መለወጧን አይቶ አዘነ፡፡
ከዚያም “እንዴት ነሽ? እህቴ ደህና ነሽ? ታመሽ እንደነበረ ሰማሁ፡፡” አላት፡፡ ከዚያም ይዞላት የመጣውን ልብሶችና ሌሎች እቃዎች ሰጣት፡፡
“የምትበይውን ሥጋ፣ ልዩ ምግብ እሰጥሻለሁ፡፡” አላት፡፡
ዴካም ህመሟ ተሻላት፡፡ ሰውነቷን ታጥባ እንደገና ደህና ሆነች፡፡ መሃመድም አብሯት ለሁለት ሳምንታት ከቆየ በኋላ ወደ እናቱ መንደር ተመልሶ ሄደ፡፡ በዚህ ጊዜ ዴካ ወዲያው እንደገና ታመመች፡፡ ሰዎቹ ሁሉ መሃመድ ሲመጣ እንደምትድንና እሱ ሲሄድ እንደምትታመም አስተዋሉ፡፡
ስለዚህ “ይህች ልጅ ምናልባትም አብራው ስላደገች አብራው መኖር ትፈልግ ይሆናል፡፡ እናም ይዟት ይሂድ፤ አዲስ ቦታም ይስማማት ይሆናል፡፡” አሉ፡፡
ዴካም ይህንን በሰማች ጊዜ በጣም ደስ አላት፡፡ አዛውንቶቹም “አብራው ልትቆይ ትችላለች፡፡ እሱም ብቸኛ ስለሆነና ገና ስላላገባ እንደ እህት ሆና ልትረዳው ትችላለች፡፡” አሉ፡፡
አፍቅራው እንደነበረ ያልጠረጠሩ ሲሆን እርሷም ፍቅሯን አልተናገረችም፡፡ በሱማሌ ባህል ልጃገረዶች (ሴት ልጆች) ፍቅራቸውን መናገር በጣም አሳፋሪ ስለሆነ ወንድ ልጆች ብቻ ናቸው ማፍቀራቸውን መናገር የሚችሉት፡፡
የመሃመድ መንደር በጣም ሩቅና በመንገዱም ላይ በአንበሶችና በሌሎች የዱር አራዊት የተሞሉ ሥፍራዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ብቻቸውን መሄድ ስለማይችሉ መሳሪያ በታጠቁ ሶስት ወንድ ልጆች ታጅበው ሄዱ፡፡ በመንገዳቸውም ላይ ዴካ አንዲት ትንሽ ጥንቸል ገድላ ለመሃመድ እየሰጠችው እግረ መንገዷን በተዘዋዋሪ በግጥም ፍቅሯን ገለፀችለት፡፡ ሌሎቹም ልጆች ፍቅሯ ገብቷቸው “መሃመድ፣ እስኪ እንምከርህ፣ ይህች ልጅ እንደምታፈቅርህ በግጥሟና ሥጋውን በሰጠችህ አኳኋን ተመልክተናል፡፡ ይህንን ሁሉ አይተናል፡፡” አሉት፡፡
እሱም ዘሎ በመነሳት “እንዴ! እህቴን እንዴት ነው የማፈቅራት? እሷስ እንዴት ልታፈቅረኝ ትችላለች? ይህ የማይሆን ነገር ነው፡፡ እኔ አብሬያት ያደኩ ወንድሟ ነኝ፡፡ ገና ትንሽ ልጅ ሆና እየረዳኋት አብረን አድገናል፡፡ እኔና እርሷ እህትና ወንድም ነን! ይህንን አይነቱን ነገር ሁለተኛ እንዳትናገሩ!” አላቸው፡፡
ይህንን ተናግሮ እንዳበቃ ዴካ ወድቃ ጭንቅላቷን ድንጋይ ስለመታው ክፉኛ ታማ መናገር ተሳናት፡፡ ወደ መሃመድ መንደርም ወሰዷት፡፡
አዛውንቶቹም ተሰብስበው “ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ምናልባት እነዚህ ልጆች በመንገድ ላይ ልጅቷን አንድ መጥፎ ነገር አድርገዋት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ልናወጣጣቸው ይገባል፡፡” አሉ፡፡
ልጆቹም “እንደሱ አይደለም፡፡ ዴካ መሃመድን እንደምታፈቅረው ስንነግረው እሱም ‘እህቴ እንዴት ልታፈቅረኝ ትችላለች?’ ማለቱን ስትሰማ ከመሬት ወድቃ ራሷ ተጎዳ እንጂ እኛ ምንም አላደረግናትም፡፡” አሉ፡፡
አንድ አዛውንትም “አሃ! አሁን ገባኝ! ይህንን ያህል ካፈቀረችው እኛ እዚህ ብናስተጫጫቸውስ?” አሉ፡፡
በዚህ ጊዜ ዴካ ነቅታ “እኚህ ሰው በጣም ጎበዝ ናቸው፡፡ ነገር ይገባቸዋል፡፡” አለች፡፡
ሌሎቹ በሙሉ በዝምታ ተዋጡ፡፡ ከዚያም አዛውንቶቹም ሁለቱ እንዲጋቡ ወስነው ከተጋቡ በኋላ ዜናው ከአምባሮ ጆሮ በደረሰ ጊዜ “እንዴ! እንዴ! እንዴት ለእኛ ሳትነግረን ይህንን ታደርጋለች? ያንን ልጅ ድሮም አልወደውም ነበር፡፡” አለች፡፡
ባሏም “አትጩሂ! ራስሽንም አትረብሺ፡፡ ይህ ልጅ ሃብትና ንብረት አለው፤ ሃብትና ንብቱንም ለሌላ ቤተሰብ ልጅ ሊሰጥ ሲል ተናደድሽ፡፡ ሁሉም ሰው ልጁን ይፈልገው ነበር፡፡ እርሱንና ከብቶቹን በቁጥጥራቸው ስር ማዋል ይፈልጉ ነበር፡፡ ዴካን ካገባት ንብረቱ ሁሉ ወዳንቺው ተመልሶ ይመጣል ማለት ነው፡፡ ከዚያም በላይ ዘመዶቹም ለጋብቻው ተጨማሪ ንብረት ይሰጡታል፡፡ አንቺም በጣም ሃብታም ከመሆንሽም በላይ እርሱም ዳግም በአንቺ ቁጥጥር ስር ይገባል፡፡” አላት፡፡ በዚህ ጊዜ እርሷም “አሃ! ትክክል ነህ፡፡ ያንን አላስተዋልኩም ነበር፡፡” በማለት በሃሳቡ ተስማማች፡፡
በዚህ ዓይነት የመሃመድ እናት ወገኖችም ለዴካ ቤተሰቦች ከብቶችና ግመሎችን ሰጧቸው፡፡ እነርሱም በጣም ሃብታምና ደስተኛ ሆኑ፡፡ ይህንን ሁሉ ሃብት እናትየው ያገኘችው በልጇ ምክንያት ነው፡፡ ወንድ ልጆች ትፈልግና ትወድ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን ሁሉ ያገኘችው በሴት ልጇ ምክንያት ነው፡፡
ወደሚቀጥለው > |
---|